የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሠራተኞችና አመራሮች በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጡ
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የፋይናንስ ቢሮ ሠራተኞችና አመራሮች በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጡ፡፡
አገልግሎቱ የተሰጠው የቤት ዕድሳት፣ አልባሳት እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የችግኝ ተከላ በማካሄድ ነው፡፡
አቶ ምሕረቱ አሰፋ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደርና ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ከተባበርን የማንሻገረው ችግር የለም ብለዋል፡፡
ኃላፊው አያይዘውም በአንድነት በመተባበራችን የህዳሴውን ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት አጠናቀናል፡፡
ጥንካሬአችንን በዓለም ሕዝብ ፊት አሳይተናል፡፡ ዛሬ ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች ችግርም ከአቅማችን በታች ነው፤ ስለዚህ አሥርና አሥራ አምስት ሆነን ብንሰባሰብ የብዙዎችን ችግር የመቅረፍ ችሎታ አለን ሲሉም አስረድተዋል ። ይህንኑ ትብብራችን ልንቀጥልበት ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ውበት አበበ የሾኔ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ዋና ተጠሪ በበኩላቸው የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ይህንን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር ይዞ ወደ ከተማችን በመንቀሳቀሱ በከተማው አስተዳደር ስም ላቅ ያለ ምሥጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡
አቶ ውበቱ አክለውም መማር እየፈለጉ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ያልቻሉትንና በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉትን ቤት በማደስና አልባሳት በመስጠት ድጋፍ በመደረጉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በተለይ ቤት የሚሠራላቸውን እማወራ ቤቱ ተጠናቆ እስከሚገቡ ድረስ ክትትል እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ምሕረቱ አሰፋ በቢሮው ሠራተኞችና አመራሮች ስም ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች የትምህርት ቁሳቁስና የብርድልብስ ስጠታዎችን አበርክተው መርሐግብሩ ተጠናቋል፡፡
ምንጭ የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ።