Habayyi hadiyyi giichi haareechi hiinchi dabasanchi ""YAAHOODE" ugudina xummine afisukkoo.
እንኳን ለሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ መላው የሀድያ ዞን፣ የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም ለሀድያ ዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን!!
የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የሀድያ ብሔር የራሱ የሆኑና ተለይተው የሚታወቅባቸው ከትዉልድ ትዉልድ ሲተላለፉ የመጡና ጠብቆ ያቆያቸው የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው፡፡
ካሉት ባህላዊ እሴቶች በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች በመታጀብ በየዓመቱ በወርሃ መስከረም (mosoro’o) በትልቅ ድምቀት የሚከበረው ያሆዴ የሀዲያ ዘመን መለወጫ ክብረ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህን ትልቅ በዓልን የብሔሩ ተወላጆች ከያሉበት በመሰባሰብ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ በየዓመቱ ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ሲከበርም በሌሎች ጊዜያት ከሚከበሩ በዓላት በተለየ መንገድ የሚከበር ሲሆን የራሱ ስርዓትና ወግ አለው፡:
የሀድያ ሕዝብ በያሆዴ በዓል በአዲስ የተስፋ ብርሃን የሚሞላበት፣ ያለፈውን ዓመት ወደማይመለስበት አሰናብቶ ለአዲሱ ዓመት ራሱን የሚያዘጋጅበት በጉጉትና በናፍቆት የሚጠበቅ ነው፡፡ ያሆዴ ከምንም በላይ ለሀዲያ ህዝብ የሁሉም ነገር መጀመሪያው ነው ተብሎ ይታመናል።
ያሆዴ የሀድያ ዘመን መለወጫ በዓል ከጭጋግና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ምዕራፍ መሻገሪያ ነው፡፡ የያሆዴ በዓል የአዲስ ዓመት ብርሃን ማብሰሪያ፣ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እርቀው የሚኖሩ ወገኖች ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ታላቅ ክብረ በዓል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ያሆዴ ለትዳር የደረሱ ወጣቶች የሚተጫጩበት የወደፊት ህይወታቸው መሠረትን የሚጥሉበት የፍቅር በዓል ነው፡፡
በዓሉ ሲከበር በርካታ የብሔሩ ማንነት፣ ታሪክ፣ ቋንቋ ፣ የአኗኗር ስርዓት ባህላዊ እሴቶች ጎልተው የሚፀባረቁበት ነው፡፡ በዓሉ የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክር አንድነትን በይበልጥ የሚያጎለብት በመሆኑ ህዝባዊ መሰረት ኖሮት ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በውስጡ አካትቶ የያዘቸው የመቻቻል፣ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ትስስርን በማጠናከር በይበልጥ ማጎልበት ይገባል፡፡
ባለፉት ዓመታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዓሉ ህዝባዊ መሰረት ኖሮት እንዲከበር የብሔሩ ባህላዊ እሴቶችን አጉልቶ በማስተዋወቅ ተለይተው እንዲታወቁ ከማድረግ አኳያ በቀጣይም ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡
ከዚህም አንፃር በዓሉን በብሔሩ ባህል ወግና ስርዓት መሠረት የበዓሉ ማክበሪያ ቦታ በ “ሀድይ ነፈራ” ሁሉንም የማህበረሰብ አካላትን ባሳተፈ እየተከበረ የመጣ ሲሆን በማክበሪያ ቦታው ባህላዊ እሴቶች የሚገልጹ የተለያዩ የልማት ግንባታ ስራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
የያሆዴን በዓል በዓለም ደረጃ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጀት ስራዎች የተጀመሩ ሲሆን በቀጣይ በሚደረገው ጥረት መላው የሀድያ ህዝብና የባህል ተቆርቋሪ የሆኑ ባለድርሻ አካላት በንቃት ተሳታፊ በመሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት ያስፈልጋል፡፡
ባህላዊ ዕሴቶቻችን የማንነታችን መገለጫዎችና የቀደምት ወገኖቻችን ውድ ስጦታዎች ናቸውና እንከባከባቸው፣ ለትውልድም እናሻግራቸው፤ መላው የዞናችን ሕዝብ በዞናችን በሚከናወኑ የልማትና ዕድገት ተግባራት እንዲሁም ሃገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ በአዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ ተቀናጅቶና ተባብሮ የመስራት ጥረቶችን ማጠናከር አለበት፡፡
በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የአካባቢያችንን ብሎም የአገራችንን ሰላምና ደህንነትን በጋራ በመጠበቅ ለሠላም ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡
በመጨረሻም ለመላው የዞናችን እና የሀገራችን ሕዝቦች በሀድያ ብሔር ዘንድ በድምቀት ለሚከበረዉ ለ 2015 ዓ.ም የ ያሆዴ በዓል እንኳን አደረሳችሁ፡፡ በዓሉ የሠላም፣ የይቅርታ፣የመተሳሰብ፣የአንድነት፣የብልጽግና ፣የጤና እና የመቻቻል እንዲሆንላችሁ በራሴና በዞኑ አስተዳደር ስም መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡
መልካም በዓል አመሰግናለሁ!
አቶ አብርሃም መጫ
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
መስከረም 11/2015 ዓ.ም