"ያሆዴ" አዲሱ ዓመት በሁሉም መስክ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ የምንተጋበት ይሁን_ አቶ ጸጋዬ ተረፈ

 

የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ተረፈ ለሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

አቶ ጸጋዬ ተረፈ የያሆዴ በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ለመላው የሀዲያ ብሔር ተወላጆች እና ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለሀዲያ የዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

የሀዲያ የዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል በየዓመቱ በወርሃ መስከረም በታላቅ ድምቀትና ባህላዊ ስርዓቶች የሚከበር ህዝባዊ በዓል ነው፡፡

በዓሉ በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ከሚታወቁ ቱባ ባህሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን በውስጡ በርካታ ገጸ በረከቶችን የያዘ ነው፡፡

ከገጸ በረከቶቹ መካከል የእርቅ ስርዓት፣ የዳኝነት ስርዓት፣ የአስተዳደር ስርዓት፣ የገበያ ስርዓት እና የሰላምና የአብሮነት እሴቶች ይገኙበታል፡፡

ከዛ ባሻገር በዓሉ አሁን ለደረስንበት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ያለው ፋይዳ እጅግ የላቀ ሲሆን በተለይም መከባበርን፣ አንድነትን፣ ሰላምን እና በጋራ ማደግን ይበልጥ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡

የያሆዴ በዓል በሀዲያ አሮጌው ዓመት ሸኝተን አዲሱን የምንቀበልበት እንደመሆኑ መጠን በአዲሱ ዓመት በሁሉም መስክ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ልንተጋ ይገባል፡፡

እንደ ዞናችን በተለይም በግብርናው መስክ እየተመዘገበ ያለውን አበረታች ውጤት በቀጣይም አጠናክሮ በማስቀጠል የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችን በመተግበር ያሉንን መልካም ዕድሎች መጠቀም ይኖርብናል፡፡ በተለይም በ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ እና ሌሎችም በግብርና መካናይዜሽን ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ልማቱን ማፋጠን ይገባል፡፡

ይህንን ትልቅ በዓል ስናከብር በብሔሩ ያሉትን ቱባ ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀምና በማልማት በይበልጥ በቀደምት አባቶች ዘንድ ለብዙ ዘመናት የአብሮነት፣ የአንድነት እና በጋራ የማደግ ተመስሳሌት ይበልጥ እንዲጎለብት እሴት ጨምረንበት መስራት ከሁላችንም ይጠበቅብናል፡፡

በቀጣይም አንድነታችንን በማጎልበት ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለንን ግንኙነትና ትስስርን በሁሉም ዘርፍ በይበልጥ በማጠንከርና በማስፋፋት ባህላችንን በማሳደግ ተያይዘን ለልማትና ዕድገት እንትጋ።

በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የብልጽግና እንዲሆን በራሴና በዞኑ ግብርና መምሪያ ስም እመኛለሁ፡፡

መልካም በዓል!!

አቶ ጸጋዬ ተረፈ

የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ

መስከረም 11/2015 ዓ.ም

Share this Post