በደቡብ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ዴላሞ ኦቶሬ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በክልሉ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል።

ከ129ሺ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና ይወስዳሉ ያሉት ኃላፊው ከዚህ ቀደም በፈተና ወቅት የሚፈጠረውን ስርቆት እና ማጭበርበር ለመከላከል ተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ስርዓት በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ መወሰኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።

ለተማሪዎች ፈተናውን በተገቢው መንገድ ለመስጠት የመኝታ፣የምግብ፣የህክምና፣የደህንነት ጉዳዮች ፣የመፈተኛ ክፍሎች፣የፈተና አስፈጻሚያዎች፣በአጠቃላይ ፈተናውን መስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል ብለዋል።

ለተማሪዎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ያለ ምንም ስጋት ፈተናውን እንዲፈተኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።በዚህም ወላጆች ምንም አይነት ስጋት እንዳያድርባቸውም ተናግረዋል።

ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ጣቢያዎች ሲመጡ እንደ ስልክ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ይዘው መምጣት እንደሌለባቸውም ዶ/ር ዲላሞ አሳስበዋል።

ከመስከረም 30/2015 ጀምሮ የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና እንደሚሰጥ የተናገሩት ኃላፊው ሁለተኛ ዙር ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ይሰጣል ብለዋል።

በክልሉ ፈተናውን በሰባት ዩኒቨርስቲዎችና በሁለት ካንፓሶች ለመስጠት ዝግጅትመደረጉን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለማድረስ የትራንስፖርት አቅርቦት የማመቻቸት ስራ መጠናቀቁንም አብራርተዋል።

ዶ/ር ዲላሞ በመግለጫቸው እንዳሉት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል።

የመማሪያ መጽሀፍትን በሶፍት ኮፒ የማሰራጨት ስራ መካሔዱን የተናገሩት ኃላፊው ከ85ሺ በላይ መምህራን ከመስከረም 27 /2015 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ስልጠና እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።በአሁኑ ሰዓት ከ1ሺ 800 በላይ ለሆኑ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንጭ:- የክልሉ ኮሙኒኬሽን

Share this Post