የክልልና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሆሳዕና ከተማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከከተማው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሄደዋል ።
የከተማው መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነሐሴ 16/2014ዓ.ም
የውይይቱ ዋና ዓላማ የህዝብ ተወካዮች በዓመት ሁለት ጊዜ የመረጣቸውን ህብረተሰብ ፊት ለፊት ቀርበው በማወያየት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መሆኑን ተገልጿል ።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ በክልል አደረጃጀት ፣ በፍትህ አሰጣጥ ፣ በመሬት አስተዳደር ፣ በአገልግሎት አሠጣጥ ፣ በገቢ አሰባሰብ ፣ በመንገድ መሠረተ -ልማትና በትምህርት ጥራት ፣ በተለይም በኑሮውድነት ፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ላነሱዋቸው ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል ።
በተጨማሪም በከተማው የሚካሄዱ መሰረተ-ልማቶች የጥራትና የፍትሃዊነት ደረጃ መጓደል፣የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት አለመስጠቱ በምሽት ለሚፈፀሙ ወንጀሎች አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።
በውይይቱ ላይ የከተማው አመራሮች ፣ የከተማው ምክር ቤት አባላት ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል ።