በ"ያሆዴ" በዓል የሀዲያ ብሔር የቤተሰብ አባላት የሚኖራቸዉ የሥራ ድርሻ በከፍል

በ"ያሆዴ" በዓል የሀዲያ ብሔር የቤተሰብ አባላት የሚኖራቸዉ የሥራ ድርሻ በከፍል

ያሆዴ በዓልን አስመልክቶ በሚኖረው ቅድመ ዝግጅት እያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት የተለያዩ የሥራ ድርሻዎች ይኖራቸዋል፡፡

· አባወራዎች፡- ለ3 እና ለ4 ወራት ያህል የመስቀል ሠንጋ በሬ ያደልባሉ፣የግጦሽ ሳር የሚያበቅል ቦታ ከልለው ያቆያሉ፡፡

በሀዲያ በያሆዴ በዓል እንኳን ሰው እንስሳም ጠግቦ ተደስቶ ነው የሚያሳልፈው፡፡ ቦታ ከልሎ ሳር እንዲያድግ የሚያደርገው ቤት ውስጥ ያሉትን እንስሳቶችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ምክኒያቱም በበዓሉ ዕለት እንሰሳትም ተከልሎ ያደገውን ሳር በልተው ጠግበው እንዲዉሉ ነው፡፡

እማወራዎች፡- ለበዓሉ የሚሆን ዝግጅት በዓሉ 3 እና 4 ወር ሲቀሩት ከወዲው እንሰት ይፍቃሉ፣ ቆጮ ፣ሜሬሮና ፣ ቡዕላን በጥንቃቄ አዘጋጅተው ያቆያሉ፡፡

ከወዲሁ የቅቤ እቁብ ዊጆ (Wijjoo) ገብተው ያዘጋጃሉ:: ለአተካና እና ስጋ ማባያ ናቀሮ /ዳጣ/ በዓይነት በዓይነት ያዘጋጃሉ፡፡ እንዲሁም በበዓሉ የሚጠጣ Aydaaraa, Dinqaa, Diqaassa [ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ] የማዘጋጀት ድርሻ የነርሱ ነው፡፡

· ወጣት ልጃገረዶች ፡- የቤቱን ወለል ቆፍረው ይደለድላሉ፣ የተለያዩ ውበት የሚሠጡ ቀለማት ያላቸው ኖራዎችን ከጫካ ፈልገው ቆፍረው በማምጣት የቤቱን ውስጥና የውጭ ግርግዳን በመቀባት የተለያዩ ጌጥ ሠርተው ያስውባሉ፡፡

· ወጣት ወንዶች ፡- በበኩላቸው ከነሐሴ ወር መግቢያ አንስተው አባቶቻቸው የሚያሳዩዋቸውን የዛፍ ግንድ ቆርጠው ይጥላሉ፡፡ ለምግብ ማብስያ እንዲሆን ፈልጠው በተለያየ ቅርፅ ደርድረው ወይም ከምረው ያደርቃሉ፡፡ Xomboraa, Saatee (ችቦ) እንጨት ከጫካ ይለቅሙና አስረው እንዲደርቅ ያስቀምጣሉ፡፡

Share this Post