"ያሆዴ" የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል በሀዲያ ዞን በምሻ ወረዳ ሞርሲጦ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

ሆሳዕና፡ መስከረም 12/01/2015 ዓ.ም

"ያሆዴ" የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የባህል ሽማግሌዎች፣ የአካባቢዉ ተወላጆች፣ ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በሞርሲጦ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የበዓሉም አከባበር የተጀመረዉ በአካባቢዉ ሽማግሌዎች ምርቃት ሲሆን አባቶችም አዲሱ ዓመት ለሀገራችን የሠላም፣ የብልፅግና፣ የመተሳሰብ የመቻቻልና የመረዳዳት እንዲሆንና የተጣሉትም በመታረቅ አዲሱ ዓመት ያሆዴ በዓል እንዲያከብሩ ጭምር አሳስበዋል።

የምሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀደቀ ጡምደዶ የያሆዴ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ያሆዴ የሀድያ ዘመን መለወጫ በዓል ከጭጋግና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ምዕራፍ መሸጋገሪያና የአዲስ ዓመት ብርሃን ማብሰሪያ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እርቀው የሚኖሩ ወገኖች ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ታላቅ ክብረ በዓል በመሆኑ ሁላችንም በዓሉን ስናከብር በአዲስ መንፈስና በመልካም ምኞት ሊናከብረዉ ይገባል ብለዋል።

የምሻ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን አበራ በዓሉ ሲከበር በርካታ የብሔሩ ማንነት፣ ታሪክ፣ ቋንቋ ፣ የአኗኗር ስርዓት ባህላዊ እሴቶች ጎልተው የሚፀባረቁበት የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክርበት እና አንድነትን በይበልጥ የሚያጎለብት በመሆኑ ህዝባዊ መሰረት ኖሮት ከትዉልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በውስጡ አካትቶ የያዘቸው የመቻቻል፣ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች ትስስርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የሀዲያን ባህል፣ እሴትና የአኗኗር ዘይቤን የሚያንፀባርቁ ባህላዊ ቁሳቁሶችም ለዕይታ ቀርበዉ በታዳሚዎች ከፍተኛ አድናቆት ተችሮባቸዋል።

በመጨረሻም የተዘጋጀዉን ችቦ(ደመራ) በመለኮስ የያሆዴ ጭፈራ በመጨፈር ወረዳዊ የያሆዴ በዓል አከባበር ፕሮግራም ተጠናቋል።

ዘገባው፦ የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ነው።

Share this Post