የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን በተመለከተ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት!!

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ ለሀዲያ ብሔር ተወላጆች፣ ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ፣ ተማሪዎች እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ ለ"ያሆዴ" በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ አበበ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም፤ ያሆዴ በዓል በሀዲያ ህዝብ ዘንድ ከሚከበሩ ቱባ ባህሎች ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ያሆዴ ከጥንቱ የሀዲያ ህዝብ ህይወት ጋር አብሮ ያደገና የመጣ ትልቅ በዓል ነው።

በዓሉ ምንም አይነት ኃይማኖታዊ ንክኪ የሌለበት፣ ሀዲያ ዘመኑን የሚቆጥርበት ትልቅ በዓል በመሆኑ ከአዲስ ተስፋ፣ ከልምላሜ፣ ለሀገር ሰላም ፀሎት ከማድረግ፣ ከብርሃን ጋር የሚገናኝ ነው።

በያሆዴ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣት ወንዶችና ሴት ልጆች ሁሉም የየራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት እና የሴቶች እኩልነት የሚረጋገጥበት፣ አቅመ ደካሞች የሚረዱበት፣ የቤተሰብ ታላቅ የሚከበርበት፣ ልጆች አባወራዎችንና እማወራዎችን የሚመረቁበት ትልቅ ተስፋ ያለ በዓል ነው።

በዓሉም የክረምቱ ጭጋ፣ ወንዝ መሙላት አልፎ በፀደይ መባቻ የሚከበር እንደመሆኑ መጠን ብሩህ ተስፋ የሰነቀ፤ የብርሃን ጮራ ያዘለ የመልካም ምኞት ማሳያ በዓል ነው ብለዋል።

ያሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብ እና በፍቅር መጪውን አድስ ዓመት በደስታ የሚቀበሉበት ልዩ የህብረተሰብ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም በዓሉ ለሀድያ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የይቅርታ፣ የአንድነት እና የጥንካሬ ተምሳሌት በመሆኑ በሀገሪቱ የማህበራዊ፣ እኮኖሚያዊ እና ፖሊቲካዊ እድገት ላይ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ስራዎች ባሻገር በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ያሆዴ በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ ሁሉም ሰው የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል ከዚያ በኃላ ሁሉም በጋራ በደስታ ያከብራል ፈጣሪን ያመሰግናል።

በመሆኑም ይህን በሀዲያ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ እድሜ ጠገብ በዓልን እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሻገር ተቋሙ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

በያሆዴ በዓል አንድነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን አባወራዎች ሰንጋ ገዝተው እማወራዎች ውጆ ገብተው ወጣቶቹ ያሆዴ ጨፍረው፣ ሴት ልጃገረዶች ቤትንና አከባቢውን በማስዋብ በቅንጅት እና እርስ በእርስ በመደጋገፍ የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡

ይህ ባህል ከህብረተሰቡ ጋር ለረዥም ዓመታት የቆየ ሲሆን በአንድነት እና በመተሳሰብ ለጋራ አላማ መቆም ድህነትን፣ ኋላቀርነትን እና በእርስ በእርስ ግኑኝነት መካከል ያለውን ልዩነት ወይም አለመግባባት ለመቅረፍ ትልቅ አቅም ስለመሆኑ ማሳያ ሆኖ ልወሰድ ይችላል።

በያሆዴ የሚታየውን የልህቀት አስተሳሰብ በመያዝ የዩኒቨርሲቲያችንን ራዕይ ለማሳካት ሁላችንም ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግና ራዕዩ ግቡን እንዲመታ መስራት በእጅጉ ያስፈልጋል።

እንደ ተቋም የሰላምና የልማት ስራዎቻችንን አጠናክረን የምናስቀጥልበት፤ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን የያሆዴ ትሩፋት በሆነው በዉይይት በመፍታት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት ልሰራ ይገባል ሲሉም ዶ/ር ሀብታሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም ያቀዳቸውን የትኩረት አቅጣጫዎችን ማለትም የአግሮፕሮሰስንግ፣ ሜዲካል ቱሪዝም፣ ታዳሽ ኃይል እና የተቀናጀ የከተማ ልማት ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ዕቅዶችን ነድፎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ፕሬዝዳንቱ ገልጸው፤ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ሁሉም የሚመለከተው አካል በቅንጅት እና በቁርጠኝነት በመስራቱ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ከሚገኝባቸው ጉዳዮች መካከል ሠላማዊ የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ማድረግ እና በተለይም የትምህርት ጥራትን እንዲሻሻል፤ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ማካሄድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠማትን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እና የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን እኩይ ሴራ በፅናት በመታገል የኢትዮጵያን አሸናፊነት እውን በማድረግ በሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋት እንድሰፍን እና ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችን እና መተሳሰባችን እንድጎለብት እመኛለሁ።

የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነው ያሆዴ በዓል የሠላም፥ የደስታ፥ የፍቅር፥ የመቻቻል፣ የልማት፣ የዕድገት እና ሀገራችን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ከስመው ብልጽግናዋ የሚረጋገጥበት ዓመት እንዲሆን ለሀዲያ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በድጋሚ መልካም በዓል!!

መስከረም ቀን 12/2015 ዓ.ም

ምንጭ የዩኒቨርስቲው የህዝብ ግንኙነት እና ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው።

Share this Post