መስከረም 30/2015 ዓ.ም (የሀዲያ ዞን መ/ኮ/ጉ/መምሪያ)
የገቢ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ለዞኑ ልማት መፋጠን የገቢ ተቋማት ተግተው መስራት እንደሚገባቸው የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ተናገሩ ።
የሀዲያ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2014 ዓ.ም ገቢ አፈጻጸምና የ2015 ዓ.ም ገቢ እቅድ ዙሪያ ከአስፈፃሚዋች ጋር በሆሳዕና ከተማ ውይይት አድርጓል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ አብርሃም መጫ ገቢ ለአንድ መንግስት መንግስት ሆኖ እንዲቀጥል ወሳኝ ተግባር መሆኑን ተናግረው።
የገቢ መውደቅ የልማት ችግር ብቻ ሳይሆን የፀጥታውም በመሆኑ የገቢ መዋቅሩ የተጣለበትን ትልቅ ሀላፊነት ተገንዝቦ በሚገባ ሊሰራ እንደሚገባው ገልፀዋል።
በመንግስት የተቀመጡ የገቢ አማራጮችን አሟጦ መጠቀም የዞኑን ልማት ማፋጠን የገቢ ተቋማት ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዋና አስተዳደሪው አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
የሀዲያ ዞን ገቢዎች ሀላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ በ2014 ዓ.ም 1 ቢሊዮን 5መቶ 44ሚሊዮን 9መቶ 17ሺ 6መቶ 13 ብር በመሰብሰብ ከእእቅድ በላይ መሠራቱን አንስተዋል።
የዞኑን የመሰብሰብ አቅም በዚህ በላይ በመሆኑ በ2015 ዓ.ም 1ቢሊዮን 8መቶ 78 ሚሊዮን ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።
በዚህም ዞኑ ካለው አቅም አንጻር ቁርጠኛ በመሆን የዞኑን የልማት ጥያቄ መመለስ በሚያስችል መልኩ የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ለመፈጸም መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መድረኩ በ2014 ዓ.ም የታዩ ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ ለመስራት የሚያስችሉ ልምዶች የተወሰደበትና አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ከግብይት ስርዓት አንፃር ደረሰኝ አሰጣጥም ሆነ አቀባበል ችግሮች መኖሩን የተናገሩት አቶ መሳይ ተገልጋዩ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምድ አነስተኛ መሆንና አንዳንድ አገልግሎት ሰጪዎች ሆን ብለው ግብርን ለማጭበርበር በሚፈጽሙት ተግባር የሚፈፀም መሆኑን አንስተዋል።
ይህንንም ለመቅረፍ ለተገልጋዮች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው።
ግብር ከፋዩ ግብርን ከመሰወር ይልቅ ግብርን በታማኝነት በመክፈል ለጋራ እድገትና ብልጽግና ከተቋሙ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የሻሾጎ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ በቀለ ዮሴፍ ለቀጣይ የ2015 ዓ.ም እቅድ ለማሳካት የነበሩ ጉድለቶች ለመቅረፍ ልምድ የተወሰደበት መሆኑን ገልፀዋል።
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሴችዱና ቀበሌ ገቢዎች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ቦጋለ ደምሴ መረጃ ገቢ የሚመነጭበትን ምንጭ ለይቶ በማወቅ መረጃ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መምሪያው የ2015ዓ.ም የአፈፃፀም ስምምነት ውል ሠነድ ላይ ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር የገቢ መዋቅር ጋር ተፈራርሟል።