የሞርሲጦ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ተመረቀ

ህዳር 01/2015 ዓ.ም (የሀዲያ ዞን መ/ኮ/ጉ/መምሪያ)

በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ የተገነባው የሞርሲጦ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ግንባታው ተጠናቅቆ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

ዛሬ የተመረቀውን የሞርሲጦ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅን ጨምሮ በክልሉ ለዓመታት ሲጓተቱ የቆዩ 12 ኘሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እየተደረጉ እንደሆነ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ገለጸ

በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ የሞርሲጡ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ በከፍተኛ መስዋዕትነት ለምረቃ በመብቃቱ ደስታዬ ወደር የለውም ያሉት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሐም መጫ ለኮሌጁ ሊሟሉ የሚገቡ ግብአቶችን በማሟላት ረገድ ዞኑ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

ኮሌጁ ዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ የራሱን አሻራ ያሳርፋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በኮሌጁ የሚወጡ ሙያተኞች ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለአካባቢው ማህበረሰብ በማቅረብ የድርሻቸው እንዲወጡ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር እንዳልካቸው ጌታቸው በበኩላቸው ባለፋት ዓመታት በነባሩ ደቡብ ክልል ስር በነበሩት በሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎችን ጨምሮ በጥቅሉ 80 የሚደርሱ ኘሮጀክቶችን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ለአገልግሎት እንዲበቁ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ክትትል ሲያደርግ እንደነበር ገልጸዋል።

ላለፋት 10 ዓመታት ግንባታቸው ሲጓተቱ የቆዩ ኘሮጀክቶች በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥረዋል ብለዋል።

ባለፈው 2014 ዓ.ም በክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ብርቱ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ 12 ኘሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ በዚህ ሰሞን ለአገልግሎት ክፍት እየተደረጉ ናቸው በማለት ተናግረዋል።

ክልሉ እነዚህ ኘሮጀክቶችን እውን በሚያደርግበት ወቅት እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበርንበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ተብሏል።

ከእነዚህ ኘሮጀክቶች አንዱ የሆነውና በሰኔ 2008 ዓ.ም በ18 ወራት ግንባታው አጠናቅቆ ለመማር ማስተማር ዝግጁ ለማድረግ በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ የሞርሲጦ ኢንደስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅ በዕቅድ ቢያዝም በተገባው ውል ተፈጻሚ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።

ግንባታውን በአንድ አመት ለማጠናቀቅ ውል የገባው ተቋራጭ በቃሉ መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ በመቻሉ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።

የግንባታው ውል በማቋረጥ በቁርጥ ዋጋ ዳግም ውል በመግባት ኮሌጁ በጥቅሉ ከ 79 ሺህ 800 ላይ ወጭ የኮሌጁ ግንባታ ተጠናቅቆ ለዛሬ ምረቃ ሊበቃ ችሏል ነው ያሉት።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪና የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አሁን ሀገራችን ለጀመረችው ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ሽግግር ይህ የሞርሲጦ ኮሌጅ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

በአካባቢው ያሉ የስንዴ የገብስና የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበርና በዘርፋ ውጤታማ ተግባር በመቀየር ሰልጣኞች ራሳቸውና አካባቢውን ለመቀየር የሚተጉበት ተቋም ሊሆን ይገባል ብለዋል ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፡፡

የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የአደረጃጀትና ርዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ኮሌጁ አዲስ እንደመሆኑ ያሉበትን የግብአት ችግሮችን ለመቅረፍ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

በህዝቡ የተነሳው የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር 3 ወረዳዎችን የሚያገናኝ በመሆኑ ጥያቄው ለፌደራል መንግስት ከቀረበ 3 ዓመታት ተቆጥሯል ብለዋል።

ይህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በጋራ እንሰራለን ብለዋል። (ደሬቴድ)

Share this Post