የሆሳዕና ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቫትና በቲኦቲ የገቢ አሰባሰብና ደረሰኝ አቆራረጥ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ከደረጃ ሀ እና ለግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ። የሆሳዕና ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

በከተማው ከስድስቱም ቀበሌ አስተዳደሮች የተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የዘርፋ ባለሙያዎችና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ ዮሐንስ እንደገለጹት በግብር አከፋፈል ዙሪያ በሚያጋጥሙ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት በቫትና በቲኦቲ ተገቢውን ደረሰኝ ካለመቁረጥ ጋር በተያያዘ ለመንግስት መግባት የነበረበት ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ህገ-ወጦች ኪስ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

አክለውም ግብር ከፋዮች ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎም ሆነ ዕቃ ሺያጭ ደረሰኝ በመስጠት ህግና መመሪያውን አክብረው የመንግስት ግብር በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የከተማው መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ሊያግዙ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀዲያ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ቅርጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ፍትሐዊ ግብር እንዲከፍል የደረሰኝ አቆራረጥ አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ከሚፈፅሙ ህገ-ወጥ ተግባራት እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል ።

የሆሳዕና ከተማ የገቢ አሰባሰብ ከሚጠበቀው በታች በሆኑን በመግለጽ አመራሩና ባለሙያው ተቀናጅቶ በዘርፉ የሚታዩትን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በመፍታት በያዝነው የጀት ዓመት ከዕቅድ በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ለሀገር ልማት ገቢ ወሳኝ መሆኑን እንደሚገነዘቡ በመጠቆም መንግስት በንግድ እንቅስቃሴ የሚፈፀሙ አሻጥሮች በመከላከል ከደረሰኝ አቆራረጥ ጋር በየደረጃው የሚያጋጥሙዋቸው ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል ።

Share this Post