ቱር ያሆዴ 2ኛውን ጉዞ በዛሬው ዕለት አድርጓል

ያሆዴ በዓልን ማስተዋወቅና ህዝባዊ መሠረትን ማጎልበት ዓላማ ያደረገው ቱር ያሆዴ 2ኛውን ጉዞ በአንሌሞ፣ ምሻና የግቤ ወረዳዎች በዛሬው ዕለት አድርጓል።

በሀዲያ ዞን አስተዳደር፣ በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያና በቱር ሃዲያ ቅንጅት እየተካሄደ የምገኘው ቱር ያሆዴ የዞኑን ባህል ቡድን ይዞ በተለያዩ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ማህበረሰባዊ ንቅናቄ እያደረገ የሚገኘው።

ያሆዴ በሁሉም የብሔሩ ተወላጆች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል እንደመሆኑ በዓሉን በሚመጥን አኳን ለማክበር የዞኑ ባህል ቡድን እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጉዞ የተደረገባቸው የወረዳዎና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ጠቁመዋል።

2ኛ ዙር ቱር ያሆዴ መነሻውን ያደረገው በዋቸሞ ዩንቨርስቲ ሲሆን የዩንቨርስቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ ለእንግዶቹ የዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የያሆዴን ማዕከል በመገንባት የሀዲያን ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ሥርዓት ለማዘመን እየሠሩ ያሉትን በርካታ ሥራዎች አስጎብኝተዋል።

በሌላ መልኩ የሀዲያ ቋንቋ እንዲበለፅግ የሀዲይሳ ትምህርት በዩኒቨርስቲው ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

አንሌሞ፣ ምሻ ፣የግቤ ወረዳዎች እና የፎንቆና የሆመቾ ከተማ አስተዳደር የባህል ቡድኑ በዛሬ ጉዞ መዳረሻውን ያደረገባቸው ሲሆን በየከተማው ሲደርሱ ታላቅ ህዝባዊ አቀባበል ተደርጎባቸዋል።

ነዋሪዎቹም በሰጡት አሰተያየት ለበዓሉ የተሰጠዉ ትኩረት የሚያስመሰግን መሆኑን በመግለፅ ተጠናክሮ መቀጠል እንደምገባ አሳስበዋል።

በቱር ያሆዴ ጉዞ በቀጣይ የሚካሄድ ሲሆኖ በዞኑ ጉዞው ያልተደረሰባቸዉ የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በኤልያስ ተሰማ

Share this Post