የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛዉ ተርባይን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት በመጀመሩ መደሳታቸዉን በሶሮ ወረዳ የሚኖሩ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ ግድቡ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ የኤሌክትሪክ ሀይል እስከሚያመነጭ ድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ለዓባይ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸዉን፣ ጉልባታቸዉንና እዉቀታቸዉን በማፍሰስ በኢትዮጵያ የጋራ ክንድ ተገድቦ ሁለተኛው ተርባይንም ሀይል በማመንጨቱ የላቀ ደስታ ተሰምቶናል ያሉት በሶሮ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌያት የሚኖሩ ህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቶ ሚሻሞ ቲራጎ፣ ወ/ሮ አመራች ቦጦሬ፣ ወ/ሮ አበበች ለዕለጎ፣ አቶ ተመስገን ዳጌቦ እና ተመስገን ሻንቆ ናቸዉ፡፡
ከዚህ በፊት አባይ በታሪክ “ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” እየተባለ ስለ አባይ ብዙ ሲዘከር፣ ሲነገር አሁን ይህ ታሪክ ተቀይሮ ዛሬ በቆራጥ ህዝቦቿ ያለማንም እገዛ በኢትዮጵዊያን ገንዘብና በደም መስዋዕትነት የተገነባ ግድብ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሥራን ከመፍጠር አኳይ ወጣቶችን ወደ ሥራ በማሰማራት ትልቅ ሚና እንደሚኖረዉ አንስተዉ ይህንንም ለመቀልበስ ከዉጭም ከዉስጥ ጠላት ሊያፈርስ ቢገዳደርም ለጠላት እጅ አልሰጥም ብላ በነገሮች ባለመሸነፍ ታሪክ የሠራችበት ዕለት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አክለዉም ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ቦንድ በመግዛትና በ8100A ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸዉን እየተወጡ እንዳሉ በመግለጽ ኢትዮጵያ በገጠማት ችግሮች መካከል እስከ ሦስተኛ ዉሃ ሙሊት በማካሂድ ሁለቱ ተርባይን 5 መቶ 40 MW ኃይል ማመጨት መጀመሩ የልፋታችን ዉጤት በባዶ አልቀረም ለወደፊትም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በወረዳዉ ባሉት አብዛኛዉ ቀበሌያት የመብራት አገልግሎት ያልደረሰበት በመሆኑ በተለይም እናቶች ለተለያዩ ስቃይና እንግልት እንደሚዳረጉ ገልፀው ለዚህም ችግር የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ሁነኛዉ መፍትሔ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ የሆኑት አቶ ደስታ ዴቶሬ እንደገለጹት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዉሃ ሙሊት ተጠናቆ ሁለተኛዉ ተርባይን ሀይል ማመንጨት በመጀመሩ ድርብ ደስታ የፈጠረ ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ዋና አስተዳደሪ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት ጅማሮ ለዜጎች ተጨባጭ ተስፋ እና ለሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ በመሆኑና ኢትዮጵያ ለአለም ማህበረሰብ ባንድራዉን ከፍ ያደረገበት ዕለት ስለሆነ የላቀ ደስታ እንደተሰማቸዉ ገልጸዋል፡፡
ዋና አስተዳደሪዉ እንደዚህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጀምሮ መጠናቀቅ ለታችኞቹ መዋቅር እንደሚቻል የሚየሳይ በመሆኑ በወረዳዉ ያሉ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ለህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ካላቸዉ በማዋጣት መንግሥት ሠራተኞችም የወር ደመወዛቸዉን በመልቀቅ ለአባይ ግድብ ግንባታ ሳይሰስቱ መስጠታቸዉን ገልፀው ግድቡ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እሰከሚሰጥ ድረስ ከጎናቸዉ እንደሚሆኑ አክለው ገልፀዋል።
ዘገበዉ የሶሮ ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ፡፡