ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ መዛግብትን መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ያሳየው እምርታ አበረታች ነው_ ቋሚ ኮሚቴው

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ መዛግብትን መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ያሳየው እምርታ አበረታች ነው_ ቋሚ ኮሚቴው

ነሐሴ 7/ 2014 ዓ.ም (የሀዲያ ዞን መ/ኮ/ጉ/መምሪያ)

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ መዛግብትን መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ያሳየው እምርታ አበረታች መሆኑን በሀዲያ ዞን ምክር ቤት የፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና የ2015 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

በመድረኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የዕውቅና እና የሽልማት መርሃግብር ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በሀዲያ ዞን ምክር ቤት የፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ኑክሮ እንዳሉት÷ የህግ የበላይነትን ማስከበር የፍትህ ተቋማት ተቀዳሚ ተግባር ነው።

ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ መዛግብትን መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ያሳየው እምርታ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በተለይም በዳኝነት ስርዓት ላይ ይታይ የነበረው የስነምግባር ጉድለት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል አሳይቷል ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ይሁንና አሁንም ፍትህን በገንዘብ በመለወጥ ፍትህን የሟጓደል አዝማሚያ እንደሚስተዋል አመላክተዋል።

ይህንንም በተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ የዳኝነት አቅምን ማጎልበትና አለፍ ሲል ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ፍትህን ለህብረተሰቡ ማስፈን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ፍርድ ቤቱ በዓመቱ በወንጀልና በፍታብሔር ከቀረበለት 15 ሺህ 5 መቶ 43 መዛግብት ውስጥ 15 ሺህ 39 መዛግብት መርምሮ ውሳኔ መሰጠቱን የገለፁት የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጥላሁን ዴታሞ።

ይህም ከባላፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ3ሺህ 337 ፋይሎች ብልጫ አለው ነው ያሉት።

በዓመቱ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልና ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እንዲሁ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ።

በዋናነት የዳኞችን የመወሰን አቅም ለማሳደግ በዓመቱ 2 ጊዜ በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የዳኞች የመወሰን አቅምና ጥራት መሻሻል አሳይቷል ነው ያሉት።

ለአብነትም በዓመቱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው መዛግብት ውስጥ 10 ሺህ 6 መቶዎቹ በሁለት ወር እና ከዛ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በዓመቱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው መዛግብት መካከል 4መቶ 42 መዛግብት ላይ ይግባኝ ተጠይቆ በ42ቱ የመሻሪያ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል። ከዚህም ውስጥ 37ቱ ተሻሽሎ ውሳኔ የተሰጠባቸው ናቸው ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የተደገፋ ከማድረግ አኳያ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የድምፅ መቅጃ መሳሪያዎች ግዢ በመፈጸም በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለቱም ወንጀል ችሎቶች አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ነው ያሉት።

ይህም በፍርድ ቤቱ ከቃል ከአመዘጋገብ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ችግርና ቅሬታ ያስቀረ ነው ብለዋል።

ይህንኑ በፍትሐብሔር ችሎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ በሁሉም የወረዳና የከተማ ፍርድ ቤቶችም የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፍርድ ቤቱን አጠቃላይ መዛግብት የሚይዝ የዳታ ቤዝ ሲስተም ለመዘርጋት መታቀዱን ጠቁመዋል።

ፍርድ ቤቱ የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

ይሁንና በአንድ ፍርድ ቤቶች የአመራር ቁርጠኝነት ችግር፣ የፍርድ ቤቶች ተግባብቶ አለመስራትና በተለያየ መልክ የሚገለጽ አድሎአዊነት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በዓመቱ ከታዩ ክፍተቶ መካከል ዋነኛዎቹ መሆናቸው ፕሬዝዳንቱ በዝርዝር አንስተዋል።

በቀጣይም ይህን ጨምሮ ፍርድ ቤቶች ተገቢ ያልሆነ ቀጠሮዎችን በመቀነስና የአገልጋይነት ስሜት በመላበስ የመወሰን አቅም ለማሳደግ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የወረዳና የከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳቶች በበኩላቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዓመቱ ከመደበኛ ድጋፍና ክትትል ባሻገር በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሰጠው ስልጠና በስራቸው ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ በዓመቱ እንደ ምስራቅ ባደዋቾና ሌሎች ፍርድ ቤቶች የጸደቀላቸው በጀት በተለያዩ ምክንያቶች መጠቀም ባለመቻላቸው በስራቸው ላይ ማነቆ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።

በቀጣይም በዚሁ መልኩ ከቀጠለ አገልግሎት መስጠት አዳጋች በመሆኑ የሚመለከታቸው አካል ችግሩን እንዲቀርፉላቸው ጠይቀዋል።

በዕለቱ በዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የዕውቅና እና የሽልማት መርሃግብር ተካሂዷል።

የግንቢቹ ከተማ ፍርድ ቤት በዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ የ1ኛ ደረጃ ተሻላሚ ሲሆን ሶሮ እና ጎንቦራ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል።

ለእያንዳንዳቸው ከ57 እሰከ 60 ሺህ ብር የሚያወጣ የፎቶ ኮፒ ማሽን እንዲሁም ዴስክቶፕ ኮምፒውተርና ፕሪንተር ማሽን ከከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ተበርክቶላቸዋል።

በይዲድያ ተስፋሁን

Share this Post