በከተማዋ ዋና መንገዶች አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ የመንገድ ዳር መብራቶች ጥገና እየተደረገላቸው ነው_ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር

መስከረም 5/2014 ዓ.ም (የሀዲያ ዞን መ/ኮ/ጉ/መምሪያ)

በሆሳዕና ከተማ ለዓመታት ተቋርጠው የቆዩ የመንገድ ዳር መብራቶች ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።

ጥገና እየተደረገባቸው የሚገኘው ከሲነዶስ ኬላ እስከ ወላይታ መውጫ ድረስ ያሉ 201 የዋና መንገድ ዳር መብራቶች መሆኑም ተጠቁሟል።

የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጀት ቤት ም/ ስራ አስኪያጅ እና የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብነት አባቢያ የመንገድ ዳር መብራት ፕሮጀክቱ በ2007 ዓ.ም በሰማል ኤሌክትሪክ መካኒካል ተቋራጭ አማካኝነት ግንባታ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ዝርጋታው ተጠናቆ በጊዜያዊ ርክብክብ ወቅት በነበሩ የቴክኒክ ችግሮች የታለመለትን አግልግሎት መስጠት ሳይችል ለዓመታት መቆየቱን አውስተዋል።

ከዚህ የተነሳ የከተማዋ ነዋሪዎች ችግሩ እንዲፈታላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለፁት ኃላፊው

የቀድሞ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም መጫን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት ችግሮቹን በመለየትና በተወሰደው ቁርጠኝነት የመንገድ ዳር መብራቶቹ በታለመላቸው ልክ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የማስቻል ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም መሠረት የጥራትና የውል ማሻሻያ በማድረግ በዛሬው ዕለት የጥገና ስራ መሰራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለማሻሻያ ስራዎች 2.8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲበቃ ይሰራል ነው ያሉት።

ይህም ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በከተማዋ የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ በምሽት እንደሚያሳለጥ ብሎም የነዋሪዎች የደህንነት ስጋትን እንደሚቀንስ አመላክተዋል።

በይዲድያ ተስፋሁን

Share this Post